እኔና ሁለቱ ወንድሞቼ ወደ ኖርዌይ የመጣነው በታህሳስ 2016 ነው። በኖርዌይ ውስጥ እንደ ሶማሊያ ሞቃት ይሆናል ብለን ስላሰብን የበጋ ልብስ ለብሰን ነበር። ይሁን እንጂ አውሮፕላን ማረፊያው ስንደርስ በረዶ ነበር። በርዶን ነበር እና አየሩ ቀዝቃዛ ነበር። ጥቂት ሻንጣዎች ብናመጣም በውስጣቸው የበጋ ልብሶች ብቻ ነበሩ።
ምንም እንኳን ቀዝቃዛ ቢሆንም ወደ ኖርዌይ ስንመጣ በጣም ደስተኛ ነበርኩ። በስተመጨረሻ ለስድስት ዓመታት ያላየኋትን እናቴን እንደገና አገኘኋት። እናቴ እና ሁለት ጓደኞቿ አገኙኝ። ባየናት ጊዜ በደስታ አለቀስን። እማማ ወደምትኖርበት ትንሽ ከተማ በመኪናም ሄድን።
የመጀመሪያዎቹ ቀናት እናቴ የምትኖርበትን ከተማ ለመልመድ ከባድ ነበር። ብርዳማ እና በረዶአማ ነበር በዛላይ ብዙም የሚታይ ነገር አልነበረም። መንገዶቹ ሙሉ በሙሉ ባዶ ነበሩ። ያገኘኋቸው ጥቂት ሰዎች ቀዝቃዛ እና የማይለመዱ ይመስሉ ነበር። በሶማሊያ በሁሉም ቦታ ሰዎች ነበሩ። ስለዚህ ሁሉም ነገር እዚህ ያልተለመደ ሆኖ ተሰማኝ። እናቴ እና ጓደኞቿ አንዳንድ ስጦታዎች ሰጡን ከዚያም የክረምት ልብስ እንድንገዛ ወሰደችን።
ከገና በዓል በኋላ በጎልማሶች ትምህርት ማእከል የኖርዌይኛ ኮርስ ተቀላቀልኩ። እዚያም መደበኛ ትምህርት ቤት ከመጀመሬ በፊት ለሁለት ዓመታት አጠናሁ። አሁን የመጨረሻ አመት ላይ ነኝ። እና ብዙ አዳዲስ ጓደኞችን አፍርቻለሁ። እኔ በጣም ተግባቢ ነኝ። እና ከሌሎች ሰዎች ጋር መገናኘት ያዝናናኛል።
ከትምህርት በኋላ በበጎ ፈቃደኞች ወደሚካሄደው ማእከል እሄዳለሁ። እዚያም በቤት ስራዎቼ ላይ እገዛ አገኛለሁ። በማዕከሉ የልብስ ስፌት ኮርስም ተቀላቅያለሁ።
በሶማሊያ ከቁርኣን ትምህርት ቤት በቀር ተምሬም ሆነ ኮርስ ወስጄ አላውቅም። ማንበብና መጻፍ አላውቅም ነበር። አሁን በሶማሊኛ እና በኖርዌጂያን ቋንቋ እና ሌሎች በርካታ ትምህርቶችን እንዴት መጻፍ እንደሚቻል ተምሬያለሁ። በፊት ያለ ትምህርት ሰው እንዳልሆንኩ ይሰማኝ ነበር። አሁን ግን ደስተኛ እና ባለዕውቀት መሆኔ ይሰማኛል።
በሚቀጥለው ዓመት በጤና እና በወጣቶች ልማት ክፍል የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን እጀምራለሁ። ወደፊት የወጣት ሰራተኛ መሆን እፈልጋለሁ። ትምህርቴን ስጨርስ ህልሜ ቋሚ ስራ ማግኘት ነው። እንዲሁም እንዴት መንዳት እንዳለብኝ መማር እና የመንጃ ፍቃድ ማግኘት እፈልጋለሁ።
ሶማሊያ ብኖር ኖሮ አሁን እናት የምሆን ይመስለኛል። ምናልባት ብዙ ልጆች ይኖሩኝ ይሆናል። ሶማሊያ ብሆን ኖሮ አሁን ያገኘሁትን አይነት እድል አላገኝም ነበር። ኖርዌይ ውስጥ በመኖሬ እድለኛ ነኝ።